Thursday, June 5, 2014

ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ሰነድ ተፈራረሙ



የህጻናትን የፍትህ አስተዳደር እና አገልግሎትን በብሔራዊ ደረጃ  ለማሻሻል የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች መካከል ተፈረመ።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህጻናት ፕሮጀክት ጽ/ቤት ያዘጋጀው የፌደራል እና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በሀገሪቱ በህጻናት ጉዳይ ላይ ወጥ አሰራርን ለመከተል የሚያስችል ሰነድ ተፈራርመዋል።

ሰነዱ በፍትህ ሥርዓት የሚያልፉ ህጻናት ነጻ የህግ፣ የማህበራዊ እና የሥነ ልቦና አገልግሎት የማግኘት መብታቸውን ለማረጋገጥ እና ወጥ አሰራርን ለመዘርጋት ያመቻል ተብሏል።
ከዚህም በለፈ ሐገር አቀፍ የፍትህ አካላት ጉባኤው ላይ በፍትህ ሂደት የሚያጋጥሙ የህጻናትን መብት እና ጥቅም ለማስከበር የተሰሩ ምርጥ ተሞክሮዎች ለልምድ ልውውጥ ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከላካይ ጠበቆች በፍትህ ሂደት የሚያልፉ ህጻናት ነጻ የህግ አገልግሎት የሚያገኙበትን አሰራር ተግባራዊ በማድረግ የሚሰጠው አገልግሎት አንዱ ምርጥ ተሞክሮ ሆኖ ቀርቧል።
ጥቃት ለደረሰባቸው ህጻናትም ይሁኑ በወንጀል ውስጥ ለተሳተፉ ህጻናት ነጻ የህግ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ የተሻለ የቅብብሎሽ አገልግሎትም በአንድ ቦታ በማቀናጀት የህጻናትን መብትንና ጥቅማቸውን ለማስከበር በሰራው ሥራ ደግሞ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ተሞክሮው ተጠቃሽ ሆኗል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላዬ አያና እንዳሉት የህጻናትን ጉዳይ ለመከታተል አንድ ማዕከል በማቋቋም ዓቃቤ ህጎቹም ሆኑ ወልጀል መርማሪ ፖሊሶቹ ሴቶች እንዲሆኑ በማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህም ህጻናት በተለይ ጥቃት ተፈጽሞባቸው ወደ ፍትህ ሥርዓቱ ሲመጡ ያለምንም ፍርሃት በግልጽ ችግራቸውን በመንገር እንዲሁም የህክምና፣ የስነ-ልቦና እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያግዛልም ብለዋል ።
የጉባኤው ተሳታፊዎችም በተለይ የህጻናትን ጉዳይ ለመከታተል የሚያስችለው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጥሩ ልምድ ያገኙበት እንደሆነ ተናግረዋል።
በጉባኤው በኢትዮጵያ የህጻናትን ልዩ መብት እና ጥቅምን ለማስከበር  ሰፊ ስራ እየተሰራ ቢሆንም በተለይ በፍትህ ሥርዓት የሚያልፉ ህጻናት መብት እና ጥቅም ለማረጋገጥ በሐገር አቀፍ ደረጃ ወጥ አሰራር አለመኖሩ እንደ ተግዳሮት ተነስቷል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ መድህን ኪሮስ የህጻናትን ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ አሁን የተፈረመው ሰነድ ፋይዳው የላቀ በመሆኑ ተፈጻሚ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

No comments:

Post a Comment