ሃያ ሦስተኛውን የኤርትራ የነፃነት በዓል ምክንያት በማድረግ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ አዲስ ሕገ መንግሥት ማርቀቅን ጨምሮ አዲስ የፖለቲካ መዋቅር ለውጥ ለማድረግ ማቀዳቸውን አስታወቁ፡፡
ፕሬዚዳንቱ የኤርትራ የነፃነት በዓል በማክበር ላይ በነበሩት በብዙ ሺሕ በሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ፊት በአስመራ ስታዲየም የኤርትራን ነፃነት አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፣ መንግሥታቸው በውስጥና በውጭ እየተሰነዘረበት ባለው ሴራ ምክንያት አዲስ የፖለቲካ አደረጃጀት ለማድረግ ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት ሴራና ጫና የአገር ግንባታ ጥረታቸው ለማሰናከል መሞከሩንም ጠቁመዋል፡፡ አገራቸው በሶማሊያና በአካባቢው ሽብርተኝነትን በመደገፏ የፀጥታው ምክር ቤት የጣለባቸው ማዕቀብም የዚሁ መሰናክል አካል እንደሆነ ለተሰበሰበው ሕዝብ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይኼ ሁሉ የተባበረ ሴራ የኤርትራን ነፃነት ትግል ውጤት ለማኮላሸትና የኤርትራ ሕዝብ እሴቶችን ለማዳከም ነው፤›› ብለዋል፡፡
በኤርትራ አዲስ የፖለቲካ ለውጥ ያመጣል የተባለውን ሰነድ ለማርቀቅ በዚሁ ዕለት በይፋ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ አዲሱ ረቂቅ ሕገ መንግሥት ኤርትራ ከውጭና ከውስጥ እየተነሱባት ካሉት ተንኮሎችና ሴራዎች ትምህርት በመውሰድ የሚረቀቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የወደፊቱን ‹‹የኤርትራ የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ አቅጣጫ ለማስያዝ አዲስ ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀመር በዚሁ አጋጣሚ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ፤›› ሲሉ የበዓሉ ታዳሚዎች ከተቀመጡበት በመነሳት ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከኤርትራ ውጪ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ግን የፕሬዚዳንቱ ንግግር ማታለያ እንደሆነ እየተናገሩ ነው፡፡
የቀይ ባህር አፋር ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀመንበር ኢብራሂም ሃሩን፣ ‹‹የኤርትራ ፕሬዚዳንት ንግግር በውሸትና በቅጥፈት የተሞላ ነው፡፡ የሕዝቡን ትግል ለማደናቀፍ የሚደረግ ጥረት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ሕዝቡን ለመሸወድና የሥልጣን ጊዜውን ለማራዘም እንጂ፣ ዛሬ ሻዕቢያ ዲሞክራሲያዊ ይሆናል የሚል እምነት የለንም፤›› ማለታቸውን የዘገበው ሪፖርተር ጋዜጣ ነው ፡፡